Wednesday, October 21, 2009

Petition To The Synod of The EOTC


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ: አሜን!

በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከምንገኝ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ተከታዮች፣

ለኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አዲስ አበባ።


ቀን፦ ጥቅምት 6/2002 .


መግቢያ


ቤተ ክርስቲያናችን መሠረቷና ጉልላቷ ክርስቶስ ሆኖ ከተመሠረተ ጀምሮ ሕዝቦቿን በፍቅር በሰላም በአንድነት ስትመራ ስለ ክርስቶስ ወንጌል እና በሰማያት ስላለው ክብር ስትመሰክር እስከ ዛሬ ደርሳለች። ሆኖም እስከ ዛሬ የደረሰችው ያለ ችግር እና ያለ ፈተና አይደለም። ታሪክ እንደሚያስታውሰን ፈተናዋ ብዙ ቢሆንም በሁሉ ላይ ሥልጣን ያለውን እግዚአብሔርን በመያዟና በትክክለኛው የእግዚአብሔር ቃል የሚሄዱ፣ ከዚህ ዓለም ተድላና ደስታ ይልቅ ለእግዚአብሔር ራሳቸውን ጃንደረባ ያደረጉ ልጆች ስለነበሯት ነው። እነርሱ ፈተናውን በመንፈሳዊ ድል አሸንፈው ለእኛ አስተላልፈውልናል።ይህም ከአባቶቻችን የተሰወረ አይደለም።


የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በክርስቶስ ወንድሞቻችን በሚሆኑ በግብጽ አባቶቻችን ተይዞ ቢቆይም በእግዚአብሔር ፈቃድ በአባቶቻችን ያላሰለሰ ጥረት ቤተ ክርስቲያን ከራሷ ልጆች ጳጳሳትን መሾም ከጀመረች ጀምሮ የማይናቁ ተግባራትን አከናውናለች። ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ ጥሩ ጥሩ የአገልግሎት ጅምሮች ቢኖሯትም እንኳን መሥራት ከሚገባት ብዙ ተግባር አኳያ ሲታይ ገና ምንም ያልተነካ እንዲያውም ለሕልውናዋ እንኳን የሚያሰጋት ፈተናዎች በተጋረጡበት ዘመን ላይ ትገኛለች።


በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ የምናያቸው ችግሮችን ለመፍታት ሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት (ምዕመናን፤ ካህናት፤ ቅዱስ ሲኖዶስ) እና በልዩ ልዩ ቦታዎች በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ያሉ ሰዎችን የሚመለከት ነው። እነዚህን አካላት ሁሉ የሚያዝዝ በቤተ ክርስቲያን ላይም ሙሉ ሥልጣን ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ ስለሆነ ቅዱስ ሲኖዶሱ ለቤተ ክርስቲያኒቱ የሚያስፈልጋትን እያቀደ ቢያዝዝ ችግሮቹ በአብዛኛው እንደሚፈቱ እናምናለን።


የዚህ ደብዳቤ ዓላማም ቤተ ክርስቲያን ያለችበትን ዘመን በመዋጀት ለምዕመናን ምሳሌ እና አርአያ በመሆን በነገር ሁሉ የሚጠበቅባትን ለመሥራት እንድትዘጋጅ እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታችን ለማሳሰብ፤ በአሁኑ ጊዜ በአባቶቻችን መካከል የተፈጠረው አለመግባባት እልባት እንዲያገኝም ለማመላከት ነው። ይህን ሐሳብ ከዚህ በታች ስማችን የተያያዘ የቤተ ክርስቲያኒቱ አማኞች ተወያይተን ያጸደቅነው ሲሆን ምንም እንኳን ሁሉንም ምዕመናን አግኝቶ ማሳተፍ ባይቻልም ይህ ሀሳብ ሀሳባቸው መሆኑን ለማወቅ አያዳግትም። በመሆኑም ቅዱስ ሲኖዶስ በሚገባ ጊዜ ሰጥቶ ይህንን ሐሳባችንን እንዲመለከትልን እና የምዕመናንን ጥያቄዎች ችላ እንዳይልብን በአክብሮት እንጠይቃለን።

ክፍል አንድ


በቅዱስ ሲኖዶስ ውስጥ ስላሉ ችግሮች


በአሁኑ ጊዜ በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት መካከል የተከሰተው ችግር ምዕመናንን በጽኑ ያሳዘነ፣ የቤተ ክርስቲያንን ጠላት ያስደሰተ፣ እግዚአብሔርን ያስቀየመ ነገር ነው። ቅዱስ ሲኖዶስ አባላቱ ብጹዓን አበው ሰዎች በመሆናቸው የሐሳብ አለመግባባት ቢፈጠር ሁሉም የተለያየ ሐሳብ ሊኖራቸው ስለሚችል አይገርመንም። ሆኖም ከቤተ ክርስቲያን ሕግ፣ ሥርዓትና ደንብ ውጭ እንዲሁም መመሪያችን ከሆነው ከእግዚአብሔር ቃልም በተቃራኒ የተፈጸሙት ነገሮች የሚያሳዝኑ እና አንገትን የሚያስደፉ እንደነበረ አባቶቻችንም ራሳችሁ የምታውቁት ጉዳይ ነው።

በመሆኑም ይህንን ችግር አስመልክቶ አቋማችንን እና ወደፊት ሊደረጉ ስለሚገባቸው ጉዳዮች እንደሚከተለው እንገልጻለን።


  1. በአባቶች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ በአንዳንድ የቤተ ክርስቲያኒቱ ጳጳሳት ላይ የተከሰተው የማስፈራራት እና የድብደባ ሙከራ ፍጹም የተወገዘ ተግባር ነው። ይህን ያደረጉ አካላትም በህግ ፊት ቀርበው እንዲጠየቁ ቤተ ክርስቲያን መንግሥትን እንድትጠይቅ፣ ቤተ ክርስቲያንም በቀኖናዋ መሰረት ተገቢውን እርምት እንድትሰጣቸው።


  1. ቤተ ክርስቲያን መንፈስ ቅዱስ በሾማቸው ጳጳሳት ብቻ እንድትመራ ፤አንዳንድ ግለሰቦች የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት እንዲቆም፤


  1. ለወደፊት በሲኖዶስ አባላት መካከል ችግር/አለመግባባት/ ቢኖር በቤተ ክርስቲያን በጸሎት እንዲታሰብ የሚደረግበት ሁኔታ እንዲመቻች፤


  1. ከቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል ማንም በስጋዊ እና በሚያስነውር ስራ ቢገኝ ቤተ ክርስቲያን በቀኖናዋ መሰረት ማረም እና ማስተካከል እንጂ ለምዕመናንም ሆነ ለማያምኑ ሰዎች አሳልፋ እንዳትሰጥ፤


  1. የቅዱስ ፓትርያርኩን ሐሳብ በተቃወሙ አንድ ሊቀ ጳጳስ ላይ የተጻፈውን ሰም አጥፊ ጽሑፍ የጻፉም ሆነ ያሰራጩ ግለሰቦች ኦርቶዶክሳውያን ከሆኑ ቤተ ክርስቲያን ባላት ሕግ መሠረት እንድትጠይቃቸው። ለወደፊትም በዚህ ዓይነት መንገድ አባቶችን ለማሳፈር እና ለማሸማቀቅ በሚሰራ ሥራ የቤተ ክርስቲያናችን ሰዎች ተባባሪ እንዳይሆኑ እንዲሁም ይህ ሥራ በይፋ እንዲወገዝ፤


  1. ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያሳልፋቸውን ውሳኔዎች የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትም ሆኑ አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ምዕመናን እንዲያከብሯቸው፤


  1. ቅዱስ ሲኖዶስ ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚመራ የመጨረሻው አካል በመሆኑ ከጊዜው ጋር እንድትራመድ የሚያደርጋትን አሠራር በውስጡ ለመዘርጋት በአንድ ልብ እና በመንፈስ ቅዱስ ለቤተ ክርስቲያን እንዲሠራ፤


  1. ቅዱስ ሲኖዶስ በራሱ አባላት መካከል ችግር ቢፈጠርበት እንኳን በሳል ሊቃውንትን እና ምዕመናንን እየጠራ እንዲያማክር እንጂ ነገሩ የማይመለከታቸው ሰዎች በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ እንዳይጋበዙ፤


  1. ማንኛውም የቤተ ክርስቲያኒቱ ጳጳስ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ሊያገኝ የሚችለውን የሕግ ከለላ እና ደኀንነት ማግኘት እንዲችል እንዲደረግ በእግዚአብሔር ስም እንጠይቃለን።


ክፍል ሁለት


በቅዱስ ሲኖዶስ እና በውጭ ያሉ አባቶችን (የቀድሞ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትን) ግንኙነት በተመለከተ


ቤተ ክርስቲያን በቅርቡ ከተከሰቱባት ታላቅ ፈተናዎች እና አሳዛኝ ጉዳዮች አንዱ በስሟ የሚጠራ ሌላ አካል መቋቋሙ ነው። ይኸውም “ስደተኛው ሲኖዶስ” በመባል የሚታወቀው እና መቀመጫውን በሰሜን አሜሪካ ያደረገው በቀድሞው ፓትርያርክ የሚመራው አካል ነው። እኛ ምዕመናን በሁለቱ አካላት መካከል የሃይማኖት ልዩነት እንደሌለ እንገነዘባለን። የሃይማኖት ልዩነት ሳይኖር በአስተዳደራዊ ችግር ምክንያት ቤተ ክርስቲያን መከፋፈሏ እኛ ምዕመናን አርአያ የምናደርገው አባት እንደሌለን ያሳየን እና አባቶች ምን ያክል ለመንጋቸው እንደአማይራሩ የሚጠቁም አሳዛኝ ድርጊት ነው። በመሆኑም ሁለቱን አካላት በተመለከተ የሚከተለውን አቋም ለቅዱስ ሲኖዶስ ለማቅረብ እንወዳለን።


  1. ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ህልውና እና ስለ ምዕመናን ሲሉ ቀርበው እንዲነጋገሩ እና ችግራቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት እንዲሞክሩ፤


  1. ሁሉም የቤተ ክርስቲየን አባቶች በመፈቃቀር እና በአንድነት ላይ የተመሠረተ አገልግሎት እንዲኖራቸው ለማድረግ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ በእግዚአብሔር ስም እንጠይቃለን።


ክፍል ሶስት


አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን ችግሮችን ስለመፍታት


ቤተ ክርስቲያናችን ቀላል የማይባሉ ችግሮች በዙሪያዋ እየተደቀኑባት ይገኛል። በመሆኑም እነዚህን ችግሮች መረዳት እና በተቻለ መጠንም መፍትሄ መስጠት ይገባል። ከዚህ በታች ያሉ ችግሮችን በጥልቀት የተወያየንባቸው ስለሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ በራሱ መፍታት የሚችላቸውን በራሱ እንዲፈታ ባይችል ግን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ችግሮችን መፍታትን እንዲቻል እንጠይቃለን።


. ከቤተ ክርስቲያኒቱ ውጭ ያሉ የቤተ ክርስቲያን ችግሮች፡ ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ ከእርሷ ውጭ ያሉ እና ቢቻል መጥፋቷን ባይቻል ደግሞ መድከሟን የሚፈልጉ አካላት መኖራቸው ግልጥ ነው። በመሆኑም ከመንግሥት ጋርም ሆነ ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ችግሮቹ የሚፈቱበት ሁኔታ እንዲመቻች እንጠይቃለን። ከችግሮቹም መካከል፦


  1. በአክራሪ ሙስሊሞች አማካይነት በምዕመናን እና በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደርሰው ትንኮሳ እንዲገታ፤


  1. ምዕመናን በእምነታቸው እንዳይኖሩ ቤተ ክርስቲያንን እምነት እና ትውፊት በአጠቃላይ የእርሷ የሆነውን ሁሉ እያጥላሉ እና እየዋሹ የሚናገሩ መናፍቃን አላግባብ ድንበር ዘለል ትችት እንዲቆም፤


  1. ቤተ ክርስቲያን በትውልዱ ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖራት ታሪክን እያዛቡ የሚያቀርቡ ግለሰቦች እና አካላት እየጨመሩ መምጣታቸው እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታችን የሚያሳስቡን ስለሆነ ችግሮቹ ትኩረት እንዲሰጣቸው በእግዚአብሔር ስም እንጠይቃለን።


. በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ያሉ የቤተ ክርስቲያን ችግሮች፦ ቤተ ክርስቲያን ከውጭ ከሚደርስባት ችግር ይልቅ ለድክመቷ እና ወደ ዃላ እንድትሄድ እያደረጋት ያለው በራሷ ቤት ውስጥ እየተፈጠሩ ያሉት ችግሮቿ ናቸው። በመሆኑም ቅዱስ ሲኖዶስ የሚከተሉትን የቤተ ክርስቲያን የውስጥ ችግሮች እንዲፈቱ የሚያደርግበትን ሁኔታ በጥልቀት እና በሰከነ መንፈስ አይቶ እንዲያሻሽል የሚከተሉትን ሐሳቦች እናቀርባለን።

  1. በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እየተፈጸሙ ያሉት የአስተዳደር ችግሮች ትኩረት እንዲሰጣቸው እና እንዲፈቱ፦ አሁን ባለው የቤተ ክርስቲያን ሁኔታ ከአንድ አጥቢያ እስከ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ድረስ ልንናገረው ከሚገባው በላይ የአስተዳደር በደል እና ሙስና እንዳለ ተረድተናል። ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ተቋም ባለ ድርሻ አካላቶቿም ብዙዎች በመሆናቸው ይህችን ታላቅ መንፈሳዊት ተቋም በሚገባ በተደራጀ እና በተጠና መንገድ ማስተዳደር ይገባል።


  1. አለመተማመን እና እርስ በእርስ መናቆር ከቤተ ክርስቲያን አገልጋይ አካላት ዘንድ እንዲጠፋ፦ ቤተ ክርስቲያን አሁን ባለችበት ደረጃ ብዙ አገልጋዮች ቢኖሯትም እርስ በእርስ አንዱ አንዱን ሲከስ ይታያል። በመሆኑም በእያንዳንዱ ቡድን መካከል ያለውን ችግር ለመፍታት ቅዱስ ሲኖዶስ ዋናው በመሆኑ ሁሉንም አገልጋዮች በፍቅር እና በአንድነት፤ በመተሳሰብ እና በመከባበር እንዲሰሩ መመሪያ እንዲሰጥ። ችግሮችም ሰፈጠሩ የሚመለከታቸውን አካላት እንዲያናግር እና እንዲያርም፤


  1. የተቀናጀ እና የተጠናከረ አሠራር አለመኖሩ፦ አገልጋዮች እርስ በእርሳቸው የሚናቆሩ በመሆናቸው፤ ቤተ ክርስቲያንን የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስም አባቶች እንደሚናገሩት በሚገባ መልኩ እየተንቀሳቀሰ ባለመሆኑ ቤተ ክርስቲያን ወጥነት ያለው እና የተቀናጀ ሥራ እየሰራች አይደለም። በዚህም በሐገር ውስጥ ደረጃ እንኳን ወጥነት ያለው እና ለትውልድ የሚተላለፍ መሰረት የሚጥል ሥራ መስራት አልተቻለም። ስለዚህ ለዚህም ተገቢው መፍትሔ እንዲሰጠው፤

ክፍል አራት

ቤተ ክርስቲያን በርእይ እና በዕቅድ እንድትሠራ ስለማድረግ


ዘመናችን በርእይ እና በዕቅድ የሚመሩበት እና ስለ እያንዳንዱ ነገርም በጥንቃቄ በመመርመር ትክክለኛውን መንገድ ችግር ካለበት እየለዩ የሚሰሩበት ጊዜ ነው። ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ተቋም እንደመሆኗ እና አገልግሎቷም ሕዝብን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ማቅረብ በመሆኑ በዕቅድ እና በርእይ ልትሠራ ይገባታል። ሁሉን ፈጻሚ እግዚአብሔር ቢሆንም ግን ቤተ ክርስቲያን የዛሬ አምስት ዓመት፤ አሥር ዓመት፤ ሃያ እና ሃምሳ ዓመት ውስጥ ልትሠራተቸው እና ልትደርስባቸው የሚገባትን ግቦች እየተለመች ልትሠራ ይገባታል። በአሁኑ ጊዜ ግን በቅርብ ያጋጠሟትን ችግሮቿን በመፍታት ላይ ያነጣጠረ ሥራ አቅዳ ልትሰራ ይገባታል።


በሁሉም አገልግሎቷ ማቀድ ቢኖርባትም እንኳን ለወደፊቷ ቤተ ክርስቲያን በጣም አስፈላጊ በሆኑ በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ አቅዳ ርዕይ እና እቅድ ኖሯት ልትሠራባቸው ይገባል እንላለን።


  1. አሁን ባለው አካሄድ ቤተ ክርስቲያን ከአስርት ዓመታት በኋላ በገጠር አካበቢ የሚረከቧትን መምህራን እና ካህናትን ማግኘት አዳጋች ይሆናል።ለዚህም ደግሞ በአሁኑ ጊዜ በየገጠሩ በአገልጋይ እጦት እየተዘጉ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ከቅዱስ ሲኖዶስ የተሰወረ አይደለም። በመሆኑም ወደ ፊት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች አገልጋዮችን እንዴት ማፍራት እንደሚቻል፤ ባይቻል ደግሞ በገጠሪቱ ያሉ ምዕመናን እንዴት ማገልገል እንዳለባት ሁኔታዎችን አይታ ልታቅድ ይገባታል።


  1. ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችንን በሀገራችን እንዳላት ምዕመና ብዛት እና ጥንታዊት እንደመሆኗ የሚጠበቀውን ያክል በማኀበራዊ ዘርፍ እየተንቀሳቀሰች አይደለም። የዚህም ምክንያት ከበጀት ጋር የተያያዘ ምክንያትም ሊኖረው እንደሚችል ማወቅ ቢቻልም የአቅሟን ያክልም እየተንቀሳቀሰች ስላልሆነ ክርስቲያናዊ ተራድዖ ኮሚሽኑ በሚገባ ተጠናክሮ ሥራውን እንዲቀጥል ቢደረግ፤ ይህንንም ከዓለም አቀፍ ለጋሾች እና ከምዕመናን ጋር በቅርበት የሚሰራበት ሁኔታ እየተጠና ታቅዶ መሠራት ይኖርበታል።


  1. ቤተ ክርስቲያን የምትኖረው በምዕመናን በሚያወጡት ስዕለት እና አስራት መሆኑ ይታወቃል። ሆኖም አሁን ካላው ኑሮ ውድነት አንጻር ምዕመናን የሚያደርጉት አስተዋፅኦ ብቻውን የካህናትን ኑሮ ደህና ደረጃ ላይ እያደረሰው አይደለም። ካህናትም በተለይ በከተማ ያሉ ካህናት ሙሉ ቀን በአገልግሎት ተጠምደው የሚኖሩ አይደሉም። በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን ካህናት ከአገልግሎታቸው በተጨማሪ አንዳንድ ሥራዎችን እንዲሰሩ የምታበረታታበት ሁኔታ እንዲመቻች የሚሆንበትን ሁኔታ እንድታቅድ።


  1. ቤተ ክርስቲያን ዘመናዊ አስተዳደርን በማስፈን አሁን እየተፈጠሩ ያሉ እንደ አላግባብ የቤተ ክርስቲያን ስራ ቅጥር፤ ገንዘብ መባከን፤ሊቃውንት ተገቢ ቦታ አለማግኘትን፤ጎቦ፤እና ሙስናን የመሳሰሉ ነገሮችን ፈጽማ መቆጣጠር፣ ማረምና ማስወገድ ይኖርባታል።


  1. ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎቷን ለራሷ ልጆች እየፈጸመች ቢሆንም እንኳን ከሀገራችን ውጭም ክርስትናውን ልታሳያቸው የሚገቡ ብዙ ሕዝቦች እና ሀገራት አሉ። በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን በሀገር ውስጥ በተጠናከረ መልኩ የምታስተምርበትን፣ ለውጭው ዓለምም ውጤት ያለው አገልግሎት አጠናክራ የምትጀምርበትን ሁኔታ ልታቅድ ይገባታል።


  1. ቤተ ክርስቲያን በራሷ ውስጥ የሚከሰቱ ጉዳዮችን በጥልቀት የሚመለከት እና ተግባራዊ ስራ የሚሰራ የህግ ክፍል እንዲኖራት ያስፈልጋል። ይህም ቤተ ክርስቲያን ከውጭ አካላት የሚሰነዘርባትን ማነኛውም ዓይነት ችግር በባለቤትነት ተከታትሎ አግባብ ባለው ህግ ፊት መብቷን የሚያሰከበር ይሆናል።ከዚህም በተጨማሪ በአብያተ ክርስቲያናት፤ በማኀበራት፤ በቀሳውስት፤ በአጠቃላይ በቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች መካከል የሚፈጠሩ ችግሮች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲፈቱ መደረግ አለበት። ይህም የቤተ ክርስቲያንን ገመና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መጨረስ ያስችላል።


  1. የቤተ ክርስቲያን አስተዳደርም ሆነ ስርዓታችን በየጊዜው ሃይማኖትን በማይቃረን መሰረት ሲኖዶስ እያየ ከጊዜው እና ከትውልዱ ጋር የሚሄድበትን መንገድ ማመቻቸት ይኖርበታል።


  1. ከውስጥም ሆነ ከውጪ የሚጠየቁ ሃይማኖታዊ ጥያቄዎችን በአግባቡና በተደራጀ መልኩ ለመመለስ የሊቃውንት ጉባዔ እንዲጠናከር፤ የሊቃውንት ጉባዔም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዓትና ትውፊት በግልጽ ለጠያቂዎች ሁሉ መመለስ እንዲችልና ተግባራዊ የሆነ ሥራ መሥራት እንዲችል እንዲደረግ፤ ማንኛውንም ሃይማኖት ነክ ጉዳዮች በተመለከተ በሙሉ ሥልጣን የሚወስንበት አሠራር እንዲመቻችለት፤ ጥናት የሚፈልጉ ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን ማጥናት እንዲችልም ሁኔታዎች እንዲመቻቹለት እንጠይቃለን።

በጠቅላላው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ራሷን ችላ፣ ራሷን አስተዳድራ፣ የራሷን ችግር በራሷ ፈትታ የተሠማራችበትን ሃይማኖታዊና ማኀበራዊ ተልእኮ እንድትወጣ ቅዱስ ሲኖዶሱ ኃላፊነቱን በሙሉ ተረክቦ እንዲሠራ እንጠይቃለን።


እግዚአብሔር ሀገራችንንና ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን ይጠብቅልን።

በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የምንገኝ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን፣

ጥቅምት 6 ቀን 2002 .


ወስብሐት ለእግዚአብሔር


PETITION-PDF-COPY



2 comments:

Unknown said...

Thank you for doing hand in hand with Christian Brothers of Dejeselam.

EthioMonitor said...

Amesegnalehu!